Wednesday, September 19, 2018

OUR UNITY IS THE KEY

ድር ቢያብር አንበሳ ያስር
እንኳን ለአዲስ ዓመት፣ በአዲስ መሪ፣ በአዲስ ለውጥና በአዲስ ፍቅር በሰላም በጤና አደረሰን!
Note: Must read where, why and how the fascinating story of Ethiopian New Year celebration all originated.
https://simenehmakonnen.blogspot.com.au/2017/09/happy-enkutatash-ethiopian-new-year-2010.html

አሁን ጭፈራውና ደስታው አለፈ። ለሚቀጥለው አዲስ ዓመት በአዲስ መንፈስ፣ በአዲስ ፍቅርና በአዲስ ሀሳብ ድልድዩን ለመገንባት እንዘጋጅ።
ለሁሉም ጊዜ አለው እንደተባለው፣ ድሮ የበላዮቻችን፣ ቤተሰቦቻችን፣ አንጋፋዎቻችን፣ የሥራ ባልደረቦቻችን፣ ጓደኞቻችንና አብሮ አደጎቻችን እንዳንናገራቸው ዝምታ ወርቅ ነው ብለውን ዛሬ ባሕላችን ሆኖ ቀረ። ንጉሥ አይከሰስ፣ ሰማይ አይታረስ ተብሎ የኖረ ሰው፣ እሱም ስልጣን ስይዝ እንደዛው ለመኖር እነደሚፈልግ መላልሰን በተግባር አይተነዋል። ይህንን የአሠራር ድንጋጌ የሚያስተጋባ የድሮ ሰው ካለ፣ ድሮ ቀረ የሚባለውን አባባል ደጋግሞ ማስተዋልም ይኖርበታል። ታዲያ ዛሬ በአዲሱ ክፍለ ዘመን ይህ ዝምታና ሁለንትናዊ አነጋገር ወደ ኋላ ከማስቀረቱም በላይ ነገራትንና ችግሮች ትዕግስትና አክብሮት በተመላበት ግልፅና ፍሬዓማ አንደበት ተወያይቶ ለየት ባለ መልኩ ለመለወጥም ሆነ ለማስወገድና ለማሸነፍ በግለሰብ፣ በማሕበራትና በሐገር ደረጃም ታምቆ የኖረው መልካምና የተሻለ ሀሳብ በየጊዜው እየፈነዳ በንዴት መልኩ በመቅረብ መሻሻልን በመፈለግ ችግር ለመፍጠር ችሏል።  
ዛሬ ደግሞ በዘር ከፋፍሎ የሰሜን ሰው፣ የደቡብ ሰው፣ የእገሌ ሰው፣ የማነህ፣ የማነሽ ብሎ ከማለያየት፣ መጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ወይም በተለምዶ አበሻ ነን ማለቱ ተገቢና በኢትዮጵያዊነት ስሜትም እንደሚያፋቅረን ጥርጥር የለውም። የትውልድ ዘር ካስፈለገም በቅንነትና በንጹህ ልቦና ያለመናናቅ መወያየትንም መቻል አስፈላጊ ነው። ማወቅ ያለብን ሁላችንም የሰው ልጆች ነን። ነገር ግን ይህ አባባል በባሕላችን ወይንም በሕብረተሰባችን ዘንድ ስላልተለመደ፣ ማንኛውንም የሰው ዘር ለማክበር ሕሊናችንን ማስተማርና መለወጥ ይኖርብናል። አእምሯችን ብዙ መጥፎ ነገሮችን ለማስወገድና ጥሩ ነገሮችን ለመማር እንደሚችል ሊቃውንቶች ደጋግመው ነግረውናል። ለመለወጥም የግል ጥንካሬንና የዘመድን፣ የጓደኛን፣ የሥራ ባልደረቦችንና የሕብረተሰባችንን ድጋፍና ተሳትፎነትም ይጠይቃል። 

ያለፈውን የአስተዳደር ጉድለትም ሆነ ከብሔር ገዢዎች ጥፋት በመማር ወደፊት እንዳይደገሙ በጥንቃቄ የተሻለ ዘዴ እንድንፈጥር ተደምረን አንድ ላይ መፍቴውን መፈለግም የሁላችንም ግዴታ ነው።
                                     
                                         አዲስ የመደመር መዝሙር
ጥፋቶች እንደነበሩ አምነንና ተቀብለን በቅን ልቦና ይቅር ተባብለንና ተባብረን በሰላም አብረን እንድንኖር በመዛለፍ ሳይሆን በየጊዜው ደጋግመን በአክብሮት መንፈስ በመወያየት መፍታትም ይኖርብናል።
ሀሳብን ከማጋራት ባሻገር መወቃቀስና እንደጠላት መተያየት የትም እንደማያደርሰንና ፍሬ ቢስ የሆነ የቂም በቀል አስተሳሰብን እንደገና ለማሰራጨት ሆን ብለው ሴራ የሚያደርጉትንም በጥሩ ልቦና ማስተዋል፣ ማዳመጥና ወደ ሰላም እንዲመለሱ ማድረግም ተገቢ መፍትሔ የሆነና በሆነ ባልሆነው ነገር በወሬ ብቻ እንደጠላት ከመተያየትም ያድነናል።
የተጀመረውም የመብትና ፍትህ እንቅስቃሴ የትግሬ፣ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ከምባታ፣ ጉራጌ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ሰሜን፣ ደቡብ፣ምዕራብ፣ ምስራቅ ጐሳ ትግል ሳይሆን፣  በአንድነት ላይ የተመረኮዘ  የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ሕልውናና ትግል መሆን እንዳለበትና የሁሉንም ጐሳ ትብብርነት የሚጠይቅ መሆኑን የማያምኑ ካሉ ሀሳባቸውን በውይይት ከተረዱ በኋላ ለመደመር እንደሚችሉ ለማድረግ በትህትና፣ ዘዴና ትዕግስት ማስረዳትንም መልመድ አለብን።
ደግሞና ደጋግሞ የሚሾሙትን፣ የገዢውን ሆነ ማንኛውንም ጐሳና ግለሰብ ያለ አግባብ መዝለፍና መሳደብ አምባገነንነት ምንም ፍሬዓማ እንዳልሆነ በተከታታይ ስላየነው፣ ነገ ሌላው ሲሾም የተለመደው እንጉርጉሮአችንና እይታችን እንዳይደጋገም አጥብቀን ማወቅም ይኖርብናል።
እስከ ዛሬ ድረስ የነበረውም የአስተዳደር ጉድለት ከነገሥታት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣና ሁሉም የሚያውቀውንና ያየውን የአሠራር ሁናቴ ያለማወቅ ከማስተጋባት በስተቀር ሆን ተብሎ ወገኑን ለመበደልና ጠላት ለማፍራት የተደረገ ሴራ እንዳልሆነም በደንብ ብናስተውል እስከዛሬ ድረስ የት በደረስን ነበር። ችግሮችን በጠብ፣ ዛቻና ጥላቻ እንደድሮ ለመፍታት እንደማንችልና ያለፈውን የአስተዳደር ሥነ ሥራዓት ለማስወገድ አዳዲስ ሀሳቦችን በየጊዜው እንዳስፈላጊነቱ ያለ ንቅፈት ማፍለቅንም መቻል አለብን። ይቻላል!እንችላለን!

መጪው ዓመትም የሰላም፣ የፍቅርና የመደመር ጊዜ፣ በቤተስብ፣ በጓደኛሞች፣ በማሕበረሰብና በአገር ደረጃ እንዲሆንልን ሁላችንም በተቻለና በተሻለ መንገድ የምንሠራበት ጊዜ ይሁንልን።
ኢትዮጵያ የሁሉም፣ ሁሉም የኢትዮጵያ !

ለቂም በቀል ሳይሆን ለለውጥ እንሥራ!
ጤናና ትዕግስቱን ይስጠን !

ከዚህ በፊት የተሰጡትን አስተያየቶች እዚህ ይመልከቱ፡

No comments: