Saturday, April 21, 2018

SOLIDARITY IS THE KEY

ለአገራችን ለውጥ ጥሩ ሀሳብ፣ምክር፣ጊዜና መተባበር ወሳኝ ናቸው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ የሚመጣው ሁላችንም በትዕግስት በመተባበር፣አዲስ የተመረጠውን ጠ/ሚ ስናከብርና ስንረዳው ብቻ ነው። አንድ ሰው ትላንትና ተመርጦ አንድ ወር እንኳን ባልሞላበት ጊዜ ውስጥ ሥር ሰዶ ለብዙ ዓመታት የቆየውን የህወሃትን/ ወያኔን አገዛዝ ደምስስ ማለት “የቸኮለች አፍሳ ለቀመች” ተረት ስለሚሆንና እንደገና ወደ ነበርንበት ማጥ ውስጥ ተመልሰን ሊያስገባን እንደሚችል ታሪካችንን መለስ ብለን መመልከት ገንቢ ሀሳብ ነው።
የአገራችን ሕዝብ ለብዙ ዘመናት በኃያላን መንግሥታት ድምፁን ሳያሰማ እንደ ሕፃን ተገዶና ታዞ ኖሯል። ከዚያም ቦኋላ ይህንን ሁሉ መጐሳቆልን ተቀብሎ ለመኖር ምርር ብሎት እንደዛሬው ቄሮ በወጣቶቻችን  በተጀመረው አድማ በ1974 ዓ ም የጦር ኃይላችን ይህን አመቺ ጊዜን ተመክቶ በኃይል የመፈንቅለ መንግሥት በማድረግ ሕዝባችንን ለአሥራ ሰባት ዓመታት በጠመንጃ በማስፈራራት ከኖረ ቦኋላ በ1991 ዓ ም በሌላው የባሰ መራራ  መሪ ህወሃት/ወያኔ በተባለው የትግራይ ብሔር ነፃ አውጪ ድርጅት ተፈነቀለ።

ህወሃትም በተራው አገራችንን በክልል በመከፋፈልና ሕዝባችንን በብሔር በመለያየት ተስማምቶ ይኖር የነበረውን ሕብረተሰብ እርስ በርስ በማጠላላትና ትዕዛዙን አልቀበልም ያለውን በመግደልና በእስር ቤት በማጐሳቆል ኑሮአቸውን ከባድ በማድረግ እስከ ዛሬ ድረስ ኖሯል።
ሕዝባችን ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በመጐሳቆልና በመገደል መኖር መሮት በዛሬው ወጣቶቻችንና ተቆርቋሪ ግልሰቦች ሕይወት መስዋዕትነት የህወሃትን/ ወያኔን አገዛዝ በመቃወም ነባሩን የኢፌዲሪ ጠ/ሚኒስቴር በበደል አኗኗርና በጭካኔ ተፅኖዎች ተገዶ ከስልጣኑ በገዛ ፈቃዱ እንዲወርድ በማስደረግ በምትኩ አዲስና ለመላው ሕዝባችን የቆመ ጠ/ሚ እንዲመረጥ በማስደረጋቸው ከልብ የመንጨ ምስጋናችን የላቀ ነው።
ይህ በዚህ እንዳለ አዲሱ ጠ/ሚ ጥልቅ የሆነ እውቀትና የሥራ ልምድ ያለው በመሆኑ ብዙ የአመራር ማስተካከያና መሻሻያ መንገዶችን በመፈለግ ላይ ሳለ ጊዜ በመስጠትና መደረግ ያለባቸውን ነገሮች በሥነ ሥርዓት፣ በአክብሮትና በትዕግስት እንደመወያየትና የሚሠሩት ልማታማ ነገሮች በሙሉ በምን ዓይነት ዘዴ የህወሃትን/ ወያኔን ነብር ሳያስደነግጡ ወይንም ጦርነት ሳያስነሱ መሠራት እንዳለባቸው በከባድ ጥንቃቄ እንዲሠራ በማድረግ ፈንታ፣ ሁለት ወር እንኳን ሳይሞላው አሁኑኑ ይህን አድርግ፣ ያን አታድርግ፣ ብሎ ብዙ ትችቶችን ከመሰንዘር መቆጠብ ለለውጡም ውጤታማ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

አቤቱታችን፣ ለብዙ ዘመናት በማንግሥታት፣ ለአሥራ ሰባት ዓመታት በደርግና ለሃያ ሰባት ዓመታት በህወሃት/ ወያኔ አገዛዝ ሥር ቆይተን ዛሬ ታዲያ ለአዲሱና ከመቼውም ጊዜ ከተሾሙት መሪዎች የሚበልጥ ጥሩ ሀሳብ ያለውና ልምድ ላለው መሪ ቢያንስ እንኳን የአንድ ዓመት ጊዜ ለምን አንሰጠውም

WEGEN TESEBSEB Gossaye Tesfaye 

ይህን ሲወርድ ሲዋረድ የወረስነውን ባህሪያችን፤መወነጃጀልን፣መነቃቀፍን፣መቀናናትን፣ተንኮለኝነትን፣አድሎነትንና ሌሎችችንም ውጤታማ ወይንም ፍሬዓማ ያልሆኑ አስተሳሰባችንን ካልለወጥን አገራችን ልትለወጥ እንደማትችል አጥብቀን ማወቅ ይኖርብናል። እንዳየነው ብዙው ትችት የሚሰነዘረውም በዲያስፖራው ካሉት ምሁሮቻችን በመሆኑም በጣም ያሳዝናል።
እራሳችን ካልተለወጥን ማንኛውንም ነገር ለመለወጥ አንችልም። ይሄም አገርን ይጨምራል።
እንደ ድሮ በሰው ማምለክና በዘመድና ጐሳ መሿሿም አከተመ። በአዲሱ ክፍለ ዘመን ማንኛውም ሰው በችሎታው እንኳን ቢመረጥ ያለትብብራችን ብቻውን እንዳፈለገው ሊያደርግ እንደማይችል ተመራጮችና መራጮች አጥብቀው ማወቅ ይኖርባቸዋል። ደግነቱ አዲሱ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ከበቂ እውቀቱ ጋር ይህንንና እዚህ ውስጥ የተጠቀሱትን ሀሳቦች በሙሉ አጥብቆ ያወቀ በመሆኑ በቅን ልቦና ከሚናገራቸው ንግግሮች መረዳት ይቻላል

BESAQ BETCAWETA MELKAMU TEBEJE

ስንት ደስታ አየን ስንት አየን መከራ፣ሲፈራረቁብን በተራ በተራ። 

ይህን ሁሉ ዓመታት ስንበደል ኖረን ዛሬ ጥሩ ለውጥ እየመጣ ሳለ፣ አሁኑኑ ካልሆነ ብለን በየቦታው ቡራከረዩ ማለታችን፣ እውር ነገ ትድናለህ ቢሉት ዛሬን እንዴት አድሬ ያለው ታሪክ ወይም ተረት በኛም ላይ ደረሰ ለማለት ያሳፍራል። ለብዙ ጊዜ ብርሃን ሳያይ የኖረው እውር፣ ዛሬን ማደር ከባድ መስሎ ታየው፣እኛም ለብዙ ዘመናትና ዓመታት ስንበደልና ስንቸገር ኖረን፣ አሁን ሙሉ በሙሉ ብርሃን ለማግኘት ጥቂት ቀናት፣ ወራት፣ ዓመት(ዓመታት)ምናልባት አንድ ዓመት ወይንም ሁለት ዓመት እስከ ምርጫ ጊዜ ድረስ መታገስ አቃተን።

ነገር ግን ምናልባት ህወሃት/ ወያኔ ችግር ከፈጠረና የአመራር ለውጦችን ለመቀበልና ከጠ/ሚሩ ጋር ለመሥራት እራስ ምታት ከሆነ እስከ ምርጫው ጊዜ ከመጠበቅ አሁኑኑ ጽንሰ ሀሳባቸው በግልጽ ከታወቀ፣ አዲሱ ጠ/ሚ ችግሩን ለሕዝቡ በመንገር ቶሎ ምርጫ እንዲደርግ ቢያደረግ ጤናማና አዲስ አመራር ያለው መንግሥት ለመመሥረት እንደሚችልና የአገራችንም ሕዝብ በተስፋ ለመኖር ይችላል። ነገር ግን ጠ/ሚሩ ምን ያህል የትዕዛዝ ኃይል እንዳለው በጉልህ ስላላየን በአሁኑ ጊዜ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው።
ያም ሆነ ይህ የምርጫ ጊዜ በቶሎ እንዲሆን ካልተሳካ ጠ/ሚሩ ለሚያሳልፋቸው ብዙ የሥራ አመራር መሻሻያዎችና የመልካም ሀሳብ ነቀፌታዎቻችንን ብቻ ሳይሆን ትዕግስታዊ ድጋፋችንንም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ይፈልጋል።
ሁላችንም የኢትዮጵያ ነን፣ ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት።
ኢትዮጵያ በሰላም ትኑር።
ቀጥለው ያንብቡ
 http://timeforchangesociety.blogspot.com/2009/07/proposition-for-all-ethiopian.html

No comments: