Saturday, October 8, 2016

BEKKA

‘በቃ’ ማለት ‘በቃ’ ነው።

እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ እስከማውቀው ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለብዙ ዘመናት ተከባብሮ፣ አንዱ ካንዱ ዘር ተፈቃቅሮ፣ ተጋብቶ፣ ተስማምቶና ሲጣላም በዘመድ እና ሽማግሌ ታርቆ የሚኖር ሕዝብ መሆኑን ነው። ብዙሃኑ ጊዜው ጋር ለመለወጥ የማይችለውን ግፍም ዝም ብሎ ተቀብሎት እንደሚኖር ነበር።
ይህ በዚህ እንዳለ አንዱ ዘር በሌላው ዘር ላይ የፈፀማቸውን የኑሮ ተፅኖና በደሎችን ምክንያት ባፌ ሙሉ ደፍሬ ለመናገር ያለአክብሮት ቢመስለኝም በድንቁርና፣ ባለማስተዋልና በግል ጥቅም ላይ የተመሠረተ፣ በጊዜው የተደራጀ የህልውና ትምህርት ባለመኖሩ፣ የስነሥርዓት አስተዳደር ጉድለትና ብዙ ኃላፊነት የተጣለባቸው የክፍለ ሀገርም ሆነ የሰፈሩ አስተማሪዎች፣ ሽማግሌዎችና የእምነት ምሁራን እምብዛም አድሎነትን ያዘለ አርአያነታቸው፣ ሀሳባቸውና አስተሳሰባቸው የሚያመጣውን ጣጣ ባለማወቅ በሕዝቡ ላይ በውድ ሳይሆን በግድ፣ በፈቃዳቸው ሳይሆን በኃይል በማስገደዳቸው ተግባራቸው በማስገደድ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ይህ ስነሥርዓት (ያላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል እንደሚባለው) እውነታዊና ሕጋዊ ባለመሆኑ በጭቆና መልክ በመታየት በመላው ሕብረተሰብ ዘንድ ለመሰራጨት በቅቷል።
ማንኛውም የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ምንም እንኳን ተፈቃቅሮና ተጋብቶ አብሮ ቢኖርም ከላይ የተጠቀሱት የስነሥርዓት ጉድለቶችና አድሎነቶች በጭቆና መልክ እንዳሉ እያወቀ የሚያሸንፍበት መንገድና እውቀት ስለተሳነው የለውጥ ጊዜ እስኪመጣለት ድረስ ከችግሩ ጋር በትዕግስት ተቆራኝቶ ኖሯል።
በማንኛውም የዓለም ሕብረተሰብ ውስጥ ጭቆና እንዳለ ያየንና የምናውቅ ግለሰቦች፣ አገራችንም ከዚህ ነፃ እንዳልሆነች አጥብቀን ያስተዋልን ሁሉ አንዱ ብሔረሰብ በሌላው ብሔረ ሰብ ስሙን፣ ባሕሉንና ሃይማኖቱን በመቀየር ሥራ ለማግኘትም ሆነ፣ በየትምህርት ቤቱ ልዩነቱንና የዘር አድሎነትን ተፅኖ ለማስወገድ፣ እኩልነትን ለመጎናፀፍ፣ የራሱንና የቤተሰቡን የኑሮ እድገት ለማሻሻል፣ በትግል የተሞላ የኑሮ አኗኗር እንደሚኖር ያለፈው ትውልድ እንደሚያውቅና አዲሱም ይህን የተወሳሰበ የአድሎነትና ዘረኝነት ቁራኛ በመገንዘብ ችግሩን በጋራ ተባብሮ የሚፈታበትን የእኩልነት መንገድ መፈለግ እንዳለበት አጥብቆ ማወቅ ይኖርበታል።
እንደ ምሳሌ ለመውሰድ ያህል፣ አንድ የኦሮሞ ብሔር የጎሳ ስም ገመቹ፣ ጫልቱ፣ ገመዳ፣ ብሪቱ፣ ወዘተ የሚባሉት በገዢው ወይንም ስልጣን ላይ ባለው ብሔር ስማቸውን ቀይረው ገብረማሪያም፣አልማዝ፣ብርሃኑ፣እልፍነሽ፣ወዘተ በመባል እንደሚኖሩ ለሁላችንም ግልፅ ነው። በተጨማሪም የእስላሙም ሆነ ማንኛውም በቁጥር አነስተኛ ብሔረሰብ በሌላው ብዛት ባለው ብሔረሰብ ውስጥ ለመኖር ስማቸውን ቀይረው እንደሚኖሩ ነው። ብርሃን ሙሐመድ፣ መስፍን አብደላ፣ራሄል ሲራጅ፣ ወዘተ የሚባሉትን በምሳሌ መልክ ለማቅረብ ይቻላል። ገብረማሪያምና ዓይናለም በመባል የተወለዱትም ብሔሮች በኋላ በደበላና ቀነኒ ቀይረው አካባቢያቸውን (ከጥቅም አንፃር) መስለው እንደሚኖሩም ተመዝግቧል።
ይህ ስምን የመለወጥ ዘገባ ከቤተመንግሥት አካባቢ እንደመነጨም ታሪክ ይነግረናል። የእቴጌ መነን አያት ንጉሥ ሚካኤል የመጀመሪያ ስማቸው ሙሐመድ ዓሊ እንደነበርና የኃይለሥላሴ አያት ፊታውራሪ ወልደሚካኤል ጉዴሳ እንደነበር፣ ልዕልት ሰብለ ደስታ፣ የኃይለ ሥላሴ የልጅ ልጅን ያገቡት ደጃዝማች ካሳ ወልደማሪያም ኦሮሞ መሆናቸውንም ታሪክ መዝግቧል። የንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ልጅ፣ የልዑል ሣኀለ ሥላሴ ባለቤት ኦሮሞ እንደሆነችና ስሟ ግን ማፀነት ሀብተማሪያም እንደሆነ ታሪክ አስተዋዮች በተጨማሪ መዝግበዋል።
በተጨማሪም በሕዝብ ብዛት አነስ ያሉት ብሔረሰቦች፤እንደ ከምባታ፣ጉራጌ፣ወላይታ፣ ወዘተ የመሳሰሉት ጐሳዎች በብዛትና በአገዛዝ አይለው በሚገኙት ብሔረሰቦች፣ በተለይም በአማራው ብሔረሰብ ተውጠው ቋንቋቸውንና ባሕላቸውን ከሞላ ጐደል መስዋዕት እንዳደረጉ ለመገንዘብና ለመረዳት የብሔሮቹን የቅርብ የኑሮ ሁናቴ ማጤን በቂ ማስረጃ እንደሆነም ባለታሪኮች ዘግበውታል።

ሕዝብ ብዛት ያላቸውም ጥቂት የኦሮሞ ጐሳዎች ሰላሳ ከመቶው ያህል የገዥው የአማራ ቋንቋና ባሕል ተፅኖ ተጭኖባቸው ባሕላቸውንና ቋንቋቸውን ሳይወዱ መስዋዕት አድርገው እንደተቀላቀሏቸውና ተመሳስለው ለመኖር እንደተገደዱ የአኗኗር ሊቃውንቶች በሰፊው ያስረዱናል።

በተጨማሪም የአማራው ብሔር ከሌላዎቹ ብሔረሰቦቻችን ባህሪና ፀባይ የተለየ መሆኑንና ሌላውን ብሔረሰባችንን በመናቅና እንደበታች እንደሚያይ የባህሪ ጥናቶች ይናገራሉ።የኦሮሞ፣ጉራጌ፣ከምባታ፣ወላይታና ሌሎችም ብሔረሰቦች የዋህና መልካም ሥነ ልቦና ያላቸው ሕዝቦች መሆናቸውን ለብዙ ዘመናት አብሯቸው የኖሩት የአማራ ቤተሰቦችና የዘር ጥናቶች ይናገራሉ። የጥላቻና መጥፎ ባህሪ በማንኛውም ሕብረተሰብ ውስጥም እንዳለ ብናውቅም በይበልጥ ጎልቶ ይታይ የነበረው መጥፎ አቀባበልና የዘረኝነት ጥላቻ ስድብ ከአማራው ብሔረሰብ በየጊዜው እንደሚሰነዘር ጥናቱ ያሳያል።አንባቢያን፣ እናንተ ወይንም ወገኖቻችሁ ባታደርጉትም ሌላው እንደሚያደርግ ሳታውቁና ሳታዩ በደፈናው እራስን ለማሞገስ አትናደዱ። ይሆን ይሆናል ብለን እናስብ። 

ይህንን ሁሉ ለማጋነንና በቅይሜታ መልክ ለማቅረብ ሳይሆን፣ ካለፈው ጥፋት ለመማርና ምን ዓይነት ታሪክ እንደነበረንና እንዴትስ የሁሉንም ብሔረ ሰብ ሰብዓዊ መብት በእኩልነት መጠበቅ እንደምንችልና ከእንደዚህ ዓይነቱ ውዝግብ እንደሚያድነን በግልፅ ማወቅ እንዳለብን ነው።
ይህንንም ሀሳቤንና የጥናት ታሪካዊ ትንተና ሳካፍል ቅያሜና ጥላቻን ለማባባስ ሳይሆን፣ ከላይ የተዘረዘሩትንና ሌሎች ጉድለቶችን በመገንዘብ ላለፈው ክረምት ቤት አይሰራም እንደሚባለው ሁሉ፣ ተጠላልተን፣ ተወነጃጅለንና ቂም በቀል እየተለዋወጥን ለመኖር ሳይሆን፣ ያለማወቅ ስህተቶች የተከሰቱ ስለሆነ ያልሰማውም፣ ያላወቀውም ሰምቶና አውቆ፣ በአንድነት የሁሉም ብሔሮች የእኩልነት መብት ተጠብቆ፣ በፊት የነበሩትንና አሁንም ያሉትን ልዩነቶችና ያስተዳደር ስህተቶችን አስተካክሎ በአንድላይ ለሁሉም ብሔር ለውጥ ለማምጣትና አብረን የምንኖርበትን ዘዴ ለመፈለግ እንዲያመች ብቻ መሆኑን በትሕትና እገልፃለሁ። በይበልጥ ለማንበብ http://timeforchangesociety.blogspot.com.au/2009/02/we-need-change-not-vengeance.html 
ይሁንና አለማወቅና ሳያውቁ ማጥፋት ኃጢአት ስለአልሆነ፣ ማመን ያቃተንና ይህ ጥፋት እንደነበር የምንክድ ግለሰቦችና ብሔረሰቦች፣ እርቅ የምትባለዋን ቅዱስ ሀሳብንም መቀበል አቅቶናል ማለት ይቻላል። ለዚህ ነው እስከ ዛሬ ድረስ ጠቅላላው ሕብረተሰባችን የሰብዓዊም ሆነ የምጣኔ ሀብት ለውጥ ከማምጣት ወደኋላ እየተጎተተ ያለው።
ነገር ግን በአሁኑ አለ የሚባለው ለውጥ አገራችንን ለውጭ አገር ሽጠን፣ ሕዝባችንን ከመሬታቸው ላይ ፈንቅለን፣ በሀብት ተሻሽለናል የሚባለው ስለሆነ፣ ይህ ለውጥ ጤናማ ስለአልሆነ እንደገና በጽሞና ብሔረሰባችን የኑሮ ሁናቴ ጋር የሚራመድ መሆኑን ማጤን ተገቢ ይመስለኛል።
ዛሬ በአገራችን ብዙ ትምህርትና እውቀት ያላቸው ሰዎች ተሟልቶ እያላት ወደኋላ የምንሄድበት/የምንመለስበት ምክንያቱ ምን ይሆንየድሮውን አስተዳደር በመከተል እኔም በተራዬ ልብላ የማለት አስተሳሰብ ያላቸው የቀድሞው ትውልዶች/ብሔሮች/መሪዎች ምክንያት ይሆንይህ ከሆነ አዲሱ ትውልድ ሊመራ የሚችልበትን ሁናቴ ለምን ለመፍጠር አልተቻለም?
በአሁኑ ግዜ የተፈጠረው የብሔረሰቦች በክልል፣ በባንዲራ፣ በመታወቂያ፣ ወዘተ መከፋፈል ሕዝባችንን ከመቼውም ይበልጥ እርስ በርስ እንዲጠላላ አድርጎታል። ይህ የአገር ውስጥ መከፋፈልም በውጪው ዓለም ለሚኖሩትም ሁሉ ከፍተኛ የስምምነት ጠንቅ ሆኖ ይገኛል።
የብሔረሰቦቻችን ባህል፣ እኩልነት፣ መብትና ህልውና የሚጠበቀው ክልል በማጠርና በመለያየት ሳይሆን መብታቸው ተጠብቆ፣ ባሕላቸውንና ቋንቋቸውን ያለምንም አድልዎ፣ ፍራቻና ተጽኖ ባሌለው መንገድ በአገር ውስጥ እየተዘዋወሩ ከማንኛውም ብሔረሰብ ጋር ስማቸውን ሳይቀይሩ ለመኖርም ሆነ ለመሥራት እንዲችሉ በማድረግ ብቻ ነው። 
ዛሬ ምስራቅንና ምዕራብ ጀርመኖችን ያለያየው ትልቁ የግርግዳ አጥር እንኳን ይቅር በማለት ከጊዜው፣ ከሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ስልጣኔ ጋር ለመራመድ አፍርሰው በአንድነት መኖር ጀምረዋል። ይህ መልካም ተግባር አንድነት ኃይል ነው የሚባለውን አባባል በደንብ የሚያፀድቅ ይመስለኛል።
ይህንንና ሌላም የሚያከፋፍሉ/የሚያለያዩ አስተሳሰቦች ላላቸው ማንኛውም ግለሰቦች/ብሔ ሰቦች፣የኢትዮጵያ ብሔረሰብ በቃ እንዳለና የሚሊኒየምን(millennium)/የአዲሱን ክፍለ ዘመን የኑሮ መብቱን በደንብ ያወቀ መሆኑን አጥብቀው ማስተዋል ይኖርባቸዋል።
ነገር ግን ይህንን መስተዋል ያላወቁ/ያወቁም ምሁሮች እኔ እሻላለሁ፣የእገሌ ልጅ ነኝ፣ ወዘተ በማለት እንደ ድሮው እራሳቸውን ከሌላው ከፍ በማድረግ ለሕብረት፣በሕብረት ለሚታገሉ የለውጥ ማህበሮች እንቅፋት መሆናቸውን በመገንዘብ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የፈራረሱትን የፖለቲካ ፓርቲዎችን መጥፎ በማስታወስ እራሳቸውን ከጥሩ ሥነ ምግባር ጋር እንዲያራምዱና መልካም ስነሥርዓትን እንዲጠብቁ የሁላችንም ምኞት እንደሆነ ነው።
ወንዝ ውኃ ወደኋላ አይፈስም እንደሚባለው ሁሉ፣ እንግዲህ ሕዝባችን ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት የሚጓጓዝበትን/የሚሻሻልበትን መንገድ/ዘዴ መፈለግ እንጂ በድሮው መንገድ/አስተሳሰብ እንደማይመራ በቃ እንዳለ አጥብቀን ማስተዋል ይኖርብናል።
ስለዚህ አዲሱ ትውልድ አገራችንን በአዲስ መንገድ/አስተሳሰብ ለመምራት ከመቼውም ይበልጥ አድሎ የሌለው ብዙ ምርጫ አለው፣ እውቀት አለው፣ አዲሱን ስልጣኔ አይቷል፣ እድልና መብት እንዳለውም ያውቃል፣ እንደ ድሮ ለመምራትም ሆነ ለመመራት እንደማይፈልግና በአንድነት ተስማምቶ ለመኖር ቆርጦ መነሳቱንም ብዙውን ጊዜ ከሚደረጉት ሰላማዊ ሰልፎች ለመረዳት ችለናል።
መልካም እድል ለሁላችን፣አገራችን ኢትዮጵያ!
አንድ ኢትዮጵያ ለሁላችን፣ ሁላችንም ለአንድ ኢትዮጵያ!
ስለዚህም ሆነ ሌላ አስተያየት በይበልጥ በድሕረ ገፄ ዲዘገባ ላይ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ:
http://timeforchangesociety.blogspot.com.au/2016/10/been-there-seen-that-part-of-that.html