ለሁሉም ጊዜ አለው እንደተባለው ሁሉ፣ ድሮ እንዳንናገራቸው ዝምታ ወርቅ ነው ብለውን ዛሬ ባሕላችን ሆኖ ቀረ። የሰው ልጅ ባኅሪ ሆኖ ሁሌ በተገናኘን ቁጥርም ምነው ጠፋህ እንባባላለን። ነገር ግን የተጠፋፋንበትን ምክንያት ከሞላ ጎደል ለምን እንደሆነም እናውቀዋለን። ይሁንና ተገናኝተን መከራከሩን፣ መጨቃጨቁን፣ ያልሆነ ወሬ መስማቱንና ማውራቱን በመጥፋትና በዝምታ እንሸፍነዋለን። እኔም በመጥፋት ግንኙነቴን ልቀይር እንጂ ያለኝን ገንቢም ሆነ ተቃራኒ ሀሳቤን ጠፍቼም ቢሆን ዝም እንዳላልኩና እንዳልሸፋፈንኩት በየጊዜው ከምታነቡት አስተያየቴ ትረዳላችሁ።
አነሰም በዛም እንደሚባለው፣ እኔ የምለው ጎበዝ፣ ያም ሆነ ይህ ዛሬ በአዲሱ ክፍለ ዘመን ይህ ዝምታ ወደ ፊት ሊያራምደን አልቻለም። ትዕግሥትና አክብሮት
በተመላበት በግልፅና በፍሬዓማ አንደበት ተወያይተን ነገራትንና ችግሮችን ለየት ባለ መልኩ ለማስወገድና ለማሸነፍ በግለሰብ፣ በማሕበራትና
በሐገር ደረጃም አስፈላጊ መሆኑን ማወቅ ተስኖን በሥልጣንና በብሔር ልዩነት ጭንቅላታችንን አበላሽተን የሌሎችንም
ከማበላሸት አልፈን የኑሮ መሰናክል በመሆን የሰውንም ሕይወት እስከማበላሸት እንደርሳለን።
በጣሙን አጥብቀን ማወቅ የተሳነን ከየትኛውም ብሔር ብንሆን በኢትዮጵያዊነታችን አምነን ኢትዮጵያዊነት አንድነታችን፣ አንድነታችን ኢትዮጵያዊነት መሆኑን ነው።
ሁሌ ያላዋቂ ሳሚ... ጥያቄዎችን በመሰንዘር የሰሜን ሰው ነህ(ሽ)? የደቡብ ሰው ነህ(ሽ)? የማነህ(ሽ)? የእገሌ ሰው? ብለን ከመለያየት፣ መጀመሪያ
ኢትዮጵያዊ(ት) ወይም በተለምዶ አበሻ ነኝ ማለቱ ያስከብራል። ከዚያ የትውልድ ዘር ካስፈለገ በቅንነትና
በንጹህ ልቦና ያለመናናቅ መወያየት ይቻላል።
ማወቅ ያለብን ሁላችንም የሰው ልጆች ነን። ነገር ግን ይህ አባባል በባሕላችን ወይንም በሕብረተሰባችን
ዘንድ የተለመደ ስላልሆነ ማንኛውንም የሰው ዘር ለማክበር ኅሊናችንን ማስተማርና መለወጥ ይኖርብናል። አእምሯችን ብዙ
መጥፎ ነገሮችን ለማስወገድና ጥሩ ነገሮችንም ለመማር (train our brain) እንደሚችል ሊቃውንቶች ደጋግመው ነግረውናል።
መስፍን ሽፈራው - ስንቱን አስታወስኩት
ፅድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም፣
ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም የሚለው የአንደኛ ደረጃ የግብረ ገብነት አስተምሪዬ መልእክት
ሁል ጊዜም ትዝ ይለኛል።
ሁሌም የምናደርገው፣ የምናየውና እምንሰማው በባሕላችን የተለመደውን
ባኅሪ ነው። ከሁሉም ጋር ለመኖር አውቀው እንዳላወቁ፣ የማያወቁት ደግሞ እንደሚያወቁ፣ተምረው እንዳልተማሩ፣ሳይማሩ እንደተማሩ፣ወደው እንዳልወደዱ፣ጠልተው እንዳልጠሉ፣አምተው እንዳላሙ፣ተሳድበው እንዳልተሳደቡና ሌላም አስተሳሰብ ወይንም አመለካከት ያላቸው ብሔረሰባችን ውስጥ ብዙ ናቸው ብል እውነቱን በማውጣቴ
ንዴትንና ጥላቻን ካባባስኩባችሁ ይቅርታ ልል ነበር ነገር ግን ምን ያለበት ዝላይ አይችልም ነው የሚብለው? እውነት ከመናገር ሌላ ያጠፋሁት ነገር የለም ለማለት ነው። ካጠፋሁ ጠቅልላውን አስተያየቴን በመስጠቴም አጥፍቻለሁ ማለት ነው እንደምታስቡት ከሆነ። ይቅርታ
ቀደም ብዬ እንዳልኳችሁ እንናገር እንጂ እንድንግባባ።
ዋናው ነገር አገራችንን ከመለወጣችን በፊት የራሳችንን አስተሳሰብና አመለካከት መለወጥ፣ እንደድሮው ማሰብን መተው፣ ዘረኝነትን ማስወገድ፣ መከባበርንና መተባበርን መልመድ፣ ቅራኔንና ጥላቻን በዱላ፣ በጠመንጃ፣ በትቺትና ወሬ ሳይሆን ችግሮችን ወይንም ጉዳዮችን በሰላምና አክብሮት ተወያይተን መፍትሄ መፈለግ ነው። ቅናትና ምቀኝነትም በዚህ በአዲሱ ክፍለ ዘመን ምንም ብንናደድ፣ብንፈነዳ እንደማይሠራ አጥብቀን ማወቅም አስፈላጊ ይመስለኛል።
መለወጥና መለወጥ እንችላለን
አብዛኛው ሕዝባችን ምን ያህል አስተሳሰቡ እንዳልተለወጠ ለማወቅ አያዳግትም፣ ምክንቱም አዲሱ
የአሠራር አስተዳደር በአዲስ መንፈስ ለመምራት በመሞከሩ ደስተኛ ያልሆኑና የድሮው አሠራር እስካሁንም ልባቸው ውስጥ ያለው ብሔረሰባችን
ሁሌም ለቅራኔና ጥላቻ ይዳረጋሉ። መፍትሄውም መጀመሪያ ራስን መለወጥና ከዚያም የሚያስፈልጉንን ነገሮች መለወጥ እንደምንችል ነው።
በጣም የሚያሳዝነውና የሚዘገንነው ነገር ቢኖር ብዙሃኑ ምሁሮቻችንም በየዕለቱ እንደ ሕፃን ቀስ
በቀስ በማደግና በመልካም አመራር ላይ ያለውን አዲሱን የአገራችንን ለውጥ እያዩ ያደጉበትን የዘወትር ትቺት ዓመል አድርገው በዘር አመካኝተው ሁሌ ያለምክንያት ሲቃረኑና ሲያንቋሽሹ መስማትና
ማየቱ ነው።
ከብዙ ዓመታት በፊት ለውጡ እንደተጀመረ ሀሳባቸውን በየጊዜው በድኅረ ገጽ ላይ አዘውትረው የሚጽፉትም
ምሁራን ወገኖቻችን በእድሜ ተሸንፈውና ምናልባት ስለ ሰለቻቸው ልበልና ከመታየትና መሰማት ተሰውረው በጤናም እንዳሉ ለማወቅ አልቻልንም። ያው የምንጠብቀው እንደ ሂሩት
በቀለ ሲሞቱ መስማቱን ነው። እስከዚያው ድረስ ግን እስከ ዛሬ ላበረከቱት አስተውጽኦ በሕይወት እያሉ ማመስገን ይኖርብናል።
ያላዋቂ ሳሚ ...እንደሚባለው ሁሉ በአመራርና በለውጡ ጥፋትም ሆነ ድክመት ካለ የሁላችንም ጥፋትና ኃላፊነት
እንደሆነም መረዳት ጥሩ ነው። ለገንቢነት የተሞከሩት የሀሳብ ጥፋቶች የበለጠ እንዲበላሹ እልህ ከማስያዝ፣ ልማቱ በይበልጥ እንዳይሻሻል ቅራኔና ያልተረጋገጠ
ወሬና ትችት ከማዘውተር፣ ማበረታቻ ሀሳብንና ምስጋናንም ማዘውተሩ ለእድገታችን ቋሚ መሰላል መሆኑን መልሰን መላልሰን መለማመድ ይኖርብናል።
ብዙ ባሕላችን ሆነው አብሮአችን ያደጉትን ፀባያችንንና ዓመላችንን ትሕትና በተሞላበትና ለየት
ባሉ በመንፈስ ተቀባይነት ባላቸው መልካም ዓመሎች ለመለወጥ በጥንካሬና በቆራጥ መንፈስ መታገል ይኖርብናል። ሕብረተሰባችንም የእያንዳንዱን ግለሰብ ለውጥ አይቶ ተቀየረ(ች)፣
ተለወጠ(ች)፣ ኮራ(ች)፣ ዘነጠ(ች)፣ ተቀየመ(ች)፣ እንደድሮ አይደለም፣ አይደለችም በማለት በአሉታዊ ምክንያቶችና ነገራት የባሰ
ከማደፍረስ የራሳችንን ፀባይ ከጊዜው ለውጥ ጋር ማስማማትን ማዘውተርና በጥሩ መንፈስም መቀበል ያስፈልገናል።
ማወቅ ያለብን ማንም ከመሬት ተነስቶ ምንም ሳያደርገው ወይንም ሳያደርጋት፣ ስለ እሱ ወይንም
እሷ ወሬም ቢወራ ሳናጣራ ሰውን የመጥላት ልማዳችንን ማቆም እንዳለብን ነው።
በደንብ ማስተዋል ያለብን ከዚህ በፊት በሥራቸውና አስተሳሰባቸው ብቁና ችሎታ የነበራቸውን መልካም ለሠሩልን ግለሰቦች ሁሉ ውለታቸውን በጥሩ ሁኔታ ማመስገን እንዳለብንም ማወቁ ጥሩ ነው። ምንም ቢሆን ምንም ማንንም በአድልዎ፣ በዘር፣ በጥላቻና ቅናት ምክንያት አስወግደን በመጥፎ አመለካከት
እንዳናይ የእያንዳንዳችን ኃላፊነትም መሆኑን ነው።
ዘመድ ከዘመዱ...ካመዱ ብለው ድሮ እንደተረቱት፣ በአሁኑ ጊዜም ልክ እንዳለፉት ዘመናት ዝምድና፣
ወገናዊነት፣ ዘርነትንና አድልዎነትን ተመርኩዘን ለማሞገስም ሆነ ለማመስገን ልዩነታችንን እናሳያለን። ይህም መስተንግዶ ከባሕላችን
የመነጨ ባኅሪ በመሆኑ፣ መንፈሳዊ አስተሳሰባቸውን ቀደም ብለው የለወጡት ግለሰቦቻችን የባሕሪውን መነሻ በደንብ ስለሚያውቁ ጥላቻ
ባለው መጥፎ አመለካከት እንደማያዩትም ደግመው ደጋግመው ከሚያደርጉት ተግባራዊ ድርጊቶች እናስተውላለን።
እንኳን ላሳደገኝ እዚህ ላደረሰኝ፣
አመሰግናለሁ ባዳው ላጐረሰኝ በማለት የአገራችን አዝማሪዎች ተጫውተዋል።
ይሁንና በትምህርት ቤትም ሆነ በቤተሰብ ደረጃ ስለእነዚህና ሌሎችም የሰላም ኑሮ ባኅሪዎች አጥብቆ
ያስተዋለና ምክር የሰጠ ምሁርና ዘመድ በጭብጥ የሚገመት ነው። እነዚህም ጥፋቶች የተዘረዘሩት ለወቀሳ ሳይሆን አብሮን ያደጉ ባኅሪዎች
መሆናቸውንና በአዲሱ ዘመንም ልብ ማለቱና ነገራትን አስተውሎ እገሌ በነገረን ወሬ ብቻ የቅርብ ጓደኞቻችንንና ሌላውንም ሰው ከመጥላታችንና
ከመራቅችን በፊት በራሳችን ኅሊና ማመዛዘንና ሳንሸበር በትዕግሥት መጠያየቅንና መወያየትን መቻል ወይንም መልመድ እንዳለብን ነው።
የእያንዳንድችን ብሔረሰብ ባኅሪና አኗኗርም የተለያየ ቢሆንም ብዙዎቻችን ካደግን በኋላ ለጥቅምና
ኑሮ ብለን ተሽሎና አይሎ በሚገኘው ብሔር ስማችንንና እምነታችንን ለውጠን እንደምንኖር ማንም ሰው እንደማይክድ ተስፋ በማድረግ ነው።
ለምሳሌ ያህል የስም ለውጥ፣ ብርሃኑ አብደላ፣ መስፍን ሁሴን፣ ወንዶሰን ገመዳ፣ አልማዝ ወልደሰናይ፣
ሐብተወልድ ጫላ፣ በዳኔ ገሠሠ፣ ወዘተ ናቸው። ይህ ለወቀሳና ለመወንጀል ሳይሆን አብሮ ለመኖር ብሔሩ የሚያደርገው የኑሮ ድርጊት ምን ያህል ተግባራዊና
የፈቃደኝነት መፍትሔ እንደሆነለት ነው።
ይህ ዛሬ በዝርዝር የፃፍኩት የአገራችን(የኢትዮጵያ) ሕዝብ የኑሮ ባኅሪም አዲስ ያልተሰማ ወሬ
መስሎ ቢታይም እውነት እንደነበረ ብዙዎቻችን ብናውቅም ተግባሩ እኔ ከሞትኩ ብዙ ዓመታት በኋላ በደንብና በተሻሻለ ሁናቴ ታሪካችን
ውስጥ ገብቶ እንደሚኖር ተስፋ አደርጋለሁ።
መሀሙድ አህመድ - ዝምታ ነው መልሴ
ሰውን ቀርበው በደንብ ሳያውቁ በደፈናው በሰሙት ወሬ ብቻ እገሌ እንደዚህ ነው፣ እንደዚህ ዓይነት
ሰው ነው፣ ወዘተ ስለተባሉ ብቻ የማያውቅትን ሰው ለመቅረብ በተወራላቸው ወሬ ጥላቻን የሚያዘወትሩ እንዳሉ የታወቀ ነው። እንደባሕል
ሆኖ ሕብረተሰባችንና ማህበረሰባችንም ወሬን በማመን ተገቢ የሆነ ያልሆነ ምክንያት ፈልፍለው መልካም ሥራ የሠሩትን ሁሉ ረስተው ሰውን
የሚነጥሉና የሚገልሉ እምብዛም ግለሰቦች እንዳሉ የማይካድ ነው።
ዶሮ ውኃ ጠምቶት መንገድ ላይ ይጠጣል፣
ከዋሉ ካደሩ መረሳት ይመጣል በማለት ንዋይ ደበበ ዘፍኖታል።
ለዚህ ነው እንኳን ጥሩ ሥራችንን ለሰው መንገር ቀርቶ ለራሳችንም ለተደረገልን ጥሩ ድርጊት
ማመስገን የሚከብደን። የዛን ሰው መጥፎም ሆነ ጥሩ ወሬ ብንሰማም ከመራቅና በግልምጫ ከማየት፣ ቀርበን መተዋወቁና መወያየቱ ብዙ
ነገሮችን ያሻሽላል፣ ያቀራርባል፣ የሁላችንንም ጥሩ ጎናችንንም ለማወቅ ያመቻል።
ሁላችንም እንደምናውቀው የሰው ልጅ በኑሮው ላይ ብዙ ችግሮችን አሸንፎ ለመኖር የሚያደርገው
ትግል ብዙ እንደሆነ ነው። ይህንንም ለማድረግ ብዙዎቹ ከሌላው ጋር ተገናኝተውና ተወያይተው ችግራቸውን ለማቃለል ሲሞክሩ፣ አንዳንዶች
ደግሞ ሌላውን ላለማስቸገር ወይንም ችግራቸውን ላለማሰራጨትና ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ልዩነታችንን ምክንያት በማድረግ ከሚያውቁትና
ከሌሎችም ርቀው በማንም ላይ የጥላቻ መንፈስ ሳይኖራቸው በሰላምና በደስታ የሚኖሩ ናቸው።
ስለራሴ ማውቀው እኔው እራሴ ነኝ፣
ለምን ዝም አይልም ሌላው ካላገዘኝ።
በማለት ድምፃዊው ንዋይ ደበበ ችግሩን በዘፈን አጋርቶናል።
ብዙም ዝርዝር ውስጥ ሳልገባ የተባለውን በሙሉ ስለምናውቅ በተቻለ ዘዴ የሰው ወሬ ሰምተን ከመለያየት
ወይንም ከመራራቅ፣ እይታችን በሞትና ሕመም ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለእያንዳንዳችን መልካም ምኞት ኖሮን የጋራ የሆነ መንፈሳዊ ሥነልቦናና
ሥነምግባር በተሞላበት ሀሳብና አስተያየት በሕይወት ተገናኝተን በጽሞና መወያየቱ ጥሩ የመቀራረብ ልምድን ሊያመጣ እንደሚችል ሙሉ
ተስፋ በማድረግ ነው።
ማወቅ እናውቃለን፣ ብንናገር እናልቃለን ማለት ቀረ። ይልቁንም በጣም የሚያሳዝነንና የሚቆጨን
ያሰብነውንና የፈለግነውን መልካም ነገር ሳናደርግና ሀሳባችንን ያለስድብ ሳንናገር መሞታችን ነው።
እንደምናውቀው የአገራችንም የብሔር የሥራ አሠራር ሁሌም አገዛዝ ወይም አስተዳደር ላይ ባሉት ብሔረ ሰቦች ሀሳብ ብቻ የተመሠረተ እንደሆነና ይህም አስተሳሰብ ሲወርድ ሲዋረድ የወረስነው የእኩልነት መብት ጠንቅ አሁንም እንዳይደገም በመደረጉ መብቱን የተነፈጉት ጥቂት ግለሰቦች ለውጡን ስላልለመዱትና ስላልተደሰቱ አምባገነን
መሆንን መርጠው ሌተቀን ከተመረጡት አዲሱ ሥርዓት መሪዎች ጋር እየታገሉ ይኖራሉ።
አባቱ ዳኛ፣ ልጁ ቀማኛ የተባለው ወገናዊ እርክብካቤ ከቀረ ብዙ ጊዜ ሆኖታል። አሁን የሥራህ
ያውጣህ/ሽ ጊዜ መሆኑን መቀበል ያቃታቸው ግለሰቦች እንዳሉ ግልጽ ነው። በያዝነው በአዲሱ ክፍለ ዘመን ሀሳባችንን ለመግለጽና ያፈለግነውን
ለማለት መብታችን ቢሆንም፣ ጥላቻና ዘረኝነትን ምርኩዝ አድርገን ሌላውን ወገኖቻችንን ዓይንህ/ሽ ላፈር ማለት ከሰብዓዊነት ውጪ ከመሆኑም
በላይ ተገቢም እንዳልሆነ በደንብ ማወቅም የውዴታ ግዴታችን ነው።
ከጊዜው ለውጥ ጋር ለመራመድም አስተሳሰባችን ካለፉት ዘመናት የተሻለና ሰብዓዊ ርኅራሄን ያዘለ
መሆን እንዳለበትና የምንኖርበት አካባቢውና ባሕሪው አመቺ ባይሆንም ለየት ባለ እሳቤ ራሳችንን ለመለወጥና ለማሻሻል ትልቅ ትዕግስትና ጊዜ
እንደሚያስፈልገን መገንዘብና ጥሩ የማስተዋል ኅሊናም እንዲኖረን ያስፈልጋል።
ሰላም ለሁላችን!