Saturday, December 28, 2019

OPPOSING & CRITICISING IS EASY…


መቃረንና መተቸት ቀላል ነው፣ ተደምሮና ተፈቃቅሮ መኖር ግን…
የኢትዮጵያዊነት አዋጅ!
እንደ ጠ/ሚኒስትራችን አብይ አህመድ አሜሪካዊው ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ስለ አሜሪካን ጥቁሮች ሰላምና ነፃነት እንደዚሁም የሰው ልጅ በሰላም አብሮ እንዲኖር በመታገሉ የኖቤል የሰላም ሽልማት በተቀበለበት ዕለት የተናገራቸው ንግግሮች ግልጽ የሆኑና እንደ አብይ አንጀት የሚያርሱ እውነታዊ አነጋገር በመሆናቸው የሚያድምጡት በሙሉ በአነጋገሩ፣ በገጸ ባሕሪውና በአቀራረቡ ተደንቀው የአዳራሹ ፀጥታ መርፌ ቢወድቅ እንደሚሰማ ያስታውቃል።
PM Abiy Ahmed Nobel Peace Prize Acceptance Speech

ከበሻሻ እስከ ባሻ፣ ከዚያም ለዓለም ማስታወሻ፣ ታዲያ ከዚህ በላይ ምን እንፈልጋለን። ይቅርታ ምን ይጠበስ ብዬ መሳደብን ባውቅም ኅሊናዬ አልፈቅድ አለኝ። ያም ሆነ ይህ እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግ አብያችንም የሰላም ሽልማቱን የተሸለመው በእንደዚህ ዓይነት አቀራርብ(ቪዲውን ተመልከቱ)ነው ሰላምን በጦርነትና በእሥራት ሳይሆን በመደመርና ፍቅር ለማምጣት ከአክራሪዎች ጋር ዘወተር በአሉባልታ ጦርነት ፍዳውን ያየው፣ አሁንም የሚያየው።
ማርቲን ሉተር ኪንግ የኖቤል ሰላም ሽልማት ሲቀበሉ የተናገሩት ንግግር (Martin Luther King Jr. Nobel Peace Prize Acceptance Speech)

በየጊዜው በድኅረ ገጾች ላይ ፍቅር የተሞላበትና ገንቢ ሀሳብ ሳይሆን አስፀያፊ ትችቶችን፣ ጥላቻና ጎሰኝነት የተሞላበት ቅራኔዎችን፣ በጣም የሚዘገንኑና ለኅሊናም ጥሩ አመለካከት ያሌላቸው፣ ለአዲሱ ትውልድም ነቀርሳ የሚሆኑ አስተሳሰቦች መሆናቸውን እናስተውላለን።
ማርቲን ሉተር ኪንግ ስለ ፍቅርና ሰላም ያለ ጦርነት ንግግር (Martin Luther King Jr.’s Peace & love without violence speech)

ብዙውን ጊዜ ልብ ብለን እንደሆነ የሚተቹትና የሚቃረኑት ግለሰቦችም ሁሌም ማማትና የመቃረን ችሎታ ያላቸውና መልካም ነገርን ለማንፀባረቅ ወይንም ለማበርከት የማይችሉ መሆናቸውን ዘወትር እናያለን። በደንብ ማወቅ ያለብን ዛሬ ስለጓደኛቸው ባሕሪና ፀባይ ውድም አድርገው ያወሩልን ሰዎች፣ ነገ ለሌላው ስለ እናንተ እንደዚሁ እንደሚያወሩ ነው። እነዚህም ሰዎች የእራሳቸውን ጥሩ የሆነ የግል አስተሳሰብ እንኳን በደንብ ለመግለፅ ስላልለመዱ ሁሌም ለኃሜትና ትችት ይዳረጋሉ። ሁላችንም ምናልባት ጥቂቶቻችን እንደምናውቀው ማንም ከአዋቂ ቤተሰብ ወይንም አዋቂ ሆኖ የተወለደ ሰው የለም።

አንዳንዶቻችን በታታሪነት እራሳችንን በበጎ ለማዋል ወይንም ለማሻሻል ትዕግስትን ተጠቅመን፣ ሁሉንም ችለን፣ ጥሩውንና መጥፍውን ለመለየት ለምደናል። የግድ ፖለቲከኛ፣ሳይንቲስት፣ ጋዜጠኛ፣ ፈላስፋ፣ በጠቅላላው ምሁር መሆን የለብንም። ፖለቲከኛውንም፣ ጋዜጠኛውንም፣ ፈላስፋውንም፣ በደፈናው የተማሩትንም ሁሉ አይተናል። ተስፋ ቆርጠው ወይንም በግዴለሽነት ላለመጨቃጨቅ ዝም ብለው የሚኖሩትንም ሁሉ እናስታውሳለን። እውነቱን ለመናገር፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በማንኛውም ጊዜ እንደ አብይ አህመድ ያለ ቅን፣ አዋቂ፣ ትሁትና ሞራሉ ከፍ ያለ አገር ወዳድ መሪ አልነበረም፣ አላየንምም። ይቅርታ ይህንንና ማንኛውንም በዚህ አስተያየት ውስጥ ያለውን ሀሳብና መልዕክት እንደችሎታቸው ያገለገሉትን መሪዎቻችንን ለማንቋሸሽና ለሠሩት ሥራ ምስጋና ቢስ ለመሆን ሳይሆን፣ ከነሱ የተሻለና ጥቅሙን ብቻ የማይፈልግ፣ የሕዝብን ስሞት የሚሰማና የሚረዳ መሪ ስለሆነ ብቻ ነው።

የጎሳ ፖለቲካና ጥላቻ እየጎላ በመታየቱም እስከዛሬ ድረስ ወደር የሌለውን ጠ/ሚ አብይ አህመድን ለምን የኖቤል የሰላም ሽልማት አገኙ ብለው የዋሁን ሕዝብ ሰብስበው እስካሁንም ድረስ የሚነጫነጩ አምባገነኖች ይስተዋላሉ። ጠ/ሚሩን እንደጥፋተኛ እንኳን ብንቆጥራቸው በዓለም ላይ አገራችንን ወክለው ለኖቤል በመቅረባቸው የመላው ሕዝባችን ድጋፍ ተገቢ እንደነበር ማሰቡ ተሳናቸው።
Silence is not golden
የዚህ ዓይነቱ የሚያሳፍር ሴራነት ባለፈው ጊዜ የገዛ ወገናችን ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሓኖም የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ኃላፊ ሆነው ከአገራችን በመመረጣቸው ብሔሩንና ከዚህ በፊት የበነበረበትን የሥራ ኃላፊነት በደንብ አልተወጣም በማለት ለሥራው እንዳይመረጥ ለዓለም ጤና ድርጅት መሥሪያ ቤት ክፍል ይግባኝ በመላክና ጩኸታቸውን ያስተጋቡ ብዙ አክቲቪስቶችን፣ ፖለቲከኞችን፣ ወዘተ አይተናል ግን አልተሳካላቸውም። እንደገና እነዚህ ሰዎች ማስተዋል የነበረባቸው የዶ/ር ቴዎድሮስን እንደ ዶ/ር አብይ ከአገራችን፣ ከአፍሪካ ለሥራው በመመረጣቸው ብቻ ትልቅ ድጋፍ በመስጠት በደስታ ተጥለቅልቀን በተቀበልን ነበር።
United, we win
ያም ሆነ ይህ በቅርብ ዘመናት ገኖ የኖረው ጎሰኝነት፣ ቅናት፣ምቀኝነት፣ ማዳላት፣ ወዘተ የመሳሰሉት ጎልተው ስለሚታዩ፣ ከዝሁ መጥፎ ሰው ሰራሽ በሽታ ለመላቀቅ ብዙ ሥራን ስለሚጠይቅ አስተሳሰባቸውን ለማሸነፍ ከመጣር ተስፋ በመቁረጥ ተቆራኝተው የሚኖሩ አሉ። ጥፋታቸውንም ስለሚያውቁ፣ ለመቀራረብ ያደረጉትና የተናገሩት መጥፎ ነገር ተጽኖው ስለከበዳቸው ላለመቅረብ እራሳቸውን የባሰ አርቀው ይገኛሉ። ጥሩ ድርጊት ያደረጉትም ሁሌ ያለ አግባብ የባኅሪ መጥፎነታቸው መወራት፣ ጎሰኝነትና ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና በመነፈጋቸው የመቀራረብ አቋማቸው ይሸረሸራል፣ ይመነምናል፣ በመጨረሻም ሰሚና አስተዋይ ሳያገኙ እንደ ተሰወሩ ይቀራሉ።
  ያ ሁሉ አለፈና መልካሙ ተበጀ

አዘም ታቀፈም…እነዚሁ ጎሰኞች፣ አምባገነኖች፣ ፖለቲከኞች፣ ጋዘጠኞችና ፈላስፋዎች ሌተ ቀን ሕዝባችንን በጥሩ አንደበታቸው ማበረታታት ተስኗቸው በመጥፎ አስተሳሰባቸው ሲበክሉና ሲበታትኑ ይስተዋላሉ። የሰው ልጅ ምንም ጥፋት እንኳን ቢኖረው ያላዋቂ ሳሚእንደሚባለው፣ እንደተማረ ሰው በትዕግስት እርማቶችንና መደረግ የሚገባቸውን ሁኔታዊ ድርጊቶች በመልካም አንደበት ማስረዳት ሲችሉ ያደጉበትና የለመዱት የሠፈር የስድብ ውርጂብኝ የሚቀናቸው መሆኑን ሁሌም መርዝ ያዘለውን አስተያየታቸውን እናስተውላለን። ይህም እንደ ትውከት በሽታ አግርሿቸው ለጊዜ እፎይ ቢሉም፣ ሕመሙ ወይንም ትውከቱ በመሰራጨት ለሎች ጠንቅ እንደሚሆንም ደንታ እንደሌላቸው ይስተዋላል። ይህ ሁሌ ቅራኔንና ጥላቻን ብቻ የማንፀባረቅ አድራጎት ወይንም ደንታቢስነት ካልተሻሻለና ሕክምና ካላገኘ፣ ልምድ ሆኖ በኑሮ ላይ ጥልቅ የሆነ የዘላለም መሰናክል እንደሚሆንም መገንዘብ አስፈላጊ ነው።  

 መደመር አስፈላጊ ነው (We must unite)
ለነቀፋ ሳይሆን ይህን በየጊዜው በመረዳትና ካየናቸው ትዝብቶች በዚህ ዓይነት ጎልቶ የሚታየውን የግለሰባችንንና የሕብረተሰባችንን ችግር በግልጽ ለማሳወቅና እነዚህም ወገኖቻችንና ግለሰቦቻችን ሁሌ የሚያደርጉትን የተደጋገመ አላስፈላጊ ትችቶቻቸውንና አሽሙሮቻቸውን በማስተዋል፣ ድርጊታቸውን ማድረግ እንደነበረባቸውና እንዳልነበረባቸው የራሳቸውን ኅሊና በመጠየቅ ዘወትር ይህንኑ ዘዴ በማዘውተር ደጋግመው እራሳቸውን በጥሩ መንፈስ ለመለወጥ ስለሚችሉ ከልብ ያለንን የግል የኅሊና ንቃት አስተሳሰብ አስተያየታችንን ስናካፍላቸው/ችሁ በደስታ ነው።
በዚህ በአዲስቷ ኢትዮጵያ ከፍለ ዘመን የሚያዋጣን ተደምረን፣ ተስማምተን፣ ተፈቃቅረን መኖር ብቻ ነው።
 
መልካም ዕድል!